Tuesday, January 22, 2013

The Future is already here!

ዘጋቢ፡-ብሥራተ ገብርኤል

የወላጆች ጥረት በቤተክርስቲያን ተቋማዊ ዝግጅት ካልተደገፈ፤ በአንጻሩም የቤተክርስቲያን ዝግጅት በወላጀቾች መንፈሳዊ እና ቤተሰባዊ ጥረት ካልታገዘ፤  ልጆቻችን የያዙትን ይለቃሉ፤ ሲከፋም ስደተኞችን ለሚያጠቃው የማንነት ቀውስ አደጋ ይጋለጣሉ...ወዘተ እያልኩ ስለ ስለቤተክርስቲያን ተቋማዊ ዝግጅት በድጋሚ እንዳስብ ያደረገኝ ይሄ ልጅ ነው፡፡

 
  
ቀኑ ቃና ዘገሊላ ነውና፤ Jan 20, 2013፤ ውጪ፤ በቤተክርስቲያኑ ዓውደ ምህረት ላይ፤ ታቦተ ህጉ እየነገሰ ነው፡፡ ካህናትም ያሬዳዊ ዜማ እና ሽብሸባ እያቀረቡ ነው፡፡ ይሄ ልጅ ደግሞ


ያለው ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ነው፡፡ የካህናቱን ዜማ እና ከበሮዋቸውን የሚሰማው በማይክራፎን ብቻ ነው እንጂ አያያቸውም፡፡ የሚሰማውንም የከበሮ ድምጽ እየተከተለ፤ ራሱን ከበሮ ያለማምዳል፡፡
ይህ ልጅ፤ ከበሮ የሚለማመደው፤ አለማማጅ ቆሞለት ወይም ወላጆቹ እንዲሞክር አዘውት አይደለም፡፡ በቦታው ከሁሉት ሕጻናት በቀር ሌላ ሰው የለም፡፡ እኔም ልጁን ያየሁት እግር ጥሎኝ ነው፡፡ ልጁ፤ በማይክራፎን የሚሰማውን ከበሮ በአንክሮ እየተከታተለ ስለነበረ፤ ቪዲዬ እየቀረጽኩት እንደሆነ እንኳን አላስተዋለም፡፡ ከታች በቪዲዬ የያዝኩትም፤ ልምምዱን ሊጨርስ አካባቢ ያለውን አፍታ ነው፡፡
የልጁን ሁኔታ ሳይ፤ The future is already here! አልኩ ለራሴ፡፡ አዎ! የወደፊቱ የቤተክርስቲያ ተስፋ፤ የዝግጅት ልምምድ ጀምሯል፡፡ ልጁ በጎ ጅምሩን እንዲጨርስ ያሉትን ተቋማት ማጠናከር፤ የሌሉትን መፍጠር እና ወላጆችን ወደ አገልግሎት መሳብ አንዱ መንገድ ነው፡፡
ይህ ድረ ገጽ፤ ቤተክርስቲያናችን፤ አዳጊ ልጆቿ፤ በጎ ጅምራቸውን አንዲጨርሱ ለማስቻል የምታደርገው ተቋማዊ ዝግጅት አንድ አካል ነው፡፡
በደብራችን በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን 115 በላይ አዳጊዎች የአማርኛ ቋንቋ፤ የሃይማኖት እና የግብረ ገብ ትምህርት እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ወላጆች፤ ልጆቻቸው በየሳምንቱ የሚማሩትን ትምህርቶች ከዚህ ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ድረ ገጽ መጠቀም ለማይችሉም ወላጆች፤ ትምህርቶችን በሰውና እና በፖስታ መልዕክት እንዲደርሳቸው የማድረግ ጥረት ተጀምሯል፡፡ ቤተክርስቲያን እንዲህ ያለ ተቋማዊ ዝግጁነቷን እንድታጠናቅቅ፤ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ትፈልጋለች፡፡ ያግኙን፤ ያነጋግሩን፤ ይርዱን፡፡
ነገ የእኛ የሚሆነው፤ ልጆቻችንን የእኛ ስናደርግ ነው፡፡ አስተያየትዎ እና ድጋፍዎ አይለየን፡፡ ወስብሀት ለእግዚአብሔር፡

No comments:

Post a Comment

እናመሰግናለን፡፡ተሳትፎዎን ይቀጥሉ፡፡

blessing

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡.......In The Name of The Father, The Son and The Holy Spirit. Amen.

Amen

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለ ወላዲቱ ድንግል፤ ወለ መስቀሉ ክቡር፤ አሜን::