Sunday, June 30, 2013

አደራ ‹‹ቅዳሴ ተማሩ››

ጓዝ ጠቆሎ፤ ከዋሽንግተን ዲ.ሲ ወደ አትላንታ መሄድ በራሱ ከባድ ቢሆንም፤ ለመምህር የሻነው ግን በጣም የከበደው፤ በሃይማኖት ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ተማሪዎቹን ትቶ መሄድ ነው፡፡ ስለዚህም፤ ዛሬ በደብሩ የአዳጊዎች ትምህርት ክፍል በተደረገለት መጠነኛ የሽኝት ስጦታ ስነስርዓት ላይ፤ መምህር የሻነው ያደረገው ስጦታችንን መቀበል ብቻ አይደለም፤ ላስተማራቸው ተማሪዎች፤ የውዳሴ ማርያም የጸሎት መጽሐፍ ስጦታ እና የ ‹‹ቅዳሴ ተማሩ›› አደራም በመስጠትም እንጂ፡፡

የፊደል ቤት የ2013 ሁለተኛ ሩብ አመት ፈተና

 የፊደል ቤት የ2013 ሁለተኛ ሩብ አመት ፈተና በ ጁን 30, 2013 እና በ ጁላይ 7, 2013 ይሰጣል፡፡ የፈተናውን ይዘት ለመመልከት ይህንን ይጫኑ፡፡

Tuesday, June 25, 2013

የመዝሙር ጥናት መርሐግብር

አዳጊ ልጆች ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራትን የሚያጠኑበት፤ ከቤተክርስቲያን የመዝሙር መሳሪያዎች፤ ሥርዓት እና ባህል ጋር የሚተዋወቁበት የትምህርት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ የአራቱ ክፍል ተማሪዎች፤ በየሳምንቱ፤ በተራ በተራ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለምዕመናን መዝሙር እንዲያቀርቡ ማስቻል የመርሐግብሩ ተጨማሪ ግብ ነው፡፡
የመዝሙ ጥናት መርሐግብሩ የሚካሄደው፤  በበጎ ፈቃደኛ የሰንበት ትምህርት መዘምራንን መምህርነት ሲሆን፤ ትምህርቱ አዳጊዎች በመደበኛነት ከሚማሩት የሃይማኖት ትምህርት ጋር ተያይዞ የሚሰጥ ሥልጠና ይሆናል፡፡
የመዝሙር ጥናት ወርኃዊ መርሐግብር፤ በዚህ ድረ ገጽ ላይ በተዘጋጀው የመዝሙር መርሐግብር ገጽ() ላይ ይለጠፋል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም፤ ሙሉ የመዝሙራት ስንኞች ይለጠፋሉ፡፡

Sunday, June 23, 2013

በኪነ ጥበቡ አየለ

ይህ ድንቅ ልጅ የሚሰራቸውን የእደ ጥበብ ውጤቶች የሚያይ ሰው በሁለት ነገር ይገረማል፤ 1ኛ. ልጁ በሚሰራቸው የእደ ጥበብ ስራዎች ጥራት 2ኛ. በልጁ የመጠሪያ ስም እና ግብር መጣጣም፡፡
ስሙ በኪነ ጥበቡ አየለ ይባላል፡፡ በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርርስቲያን የመሠረተ ሃይማኖት ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በኪነ ጥበቡ ካለው ጨዋ ስነምግባር እና የቤተክርስቲያን ፍቅር በተጨማሪ፤ ኢትዬጵያዊ ባሕሉን እና ታሪኩን የሚያንጸባርቁ የእደ ጥበብ ስራዎችን ይሰራል፡፡
በኪነጥበቡ አየለ ከጥበብ ሥራዎቹ ጋር
በኪነጥበቡ አየለ እና ዘማሪ የሻነው መኮንን
ከአሁን በፊት የቅዱስ ላሊበላን ሕንጻ ሞዴል ሰርቶ ያሳየው ይህ አዳጊ፤ ዛሬ ደግሞ በቤተክርስቲያናችን እና በኢትዬጵያዊ ባህላችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን የሙዚቃ መሳሪያ ክራር ሞዴል ሰርቶ አሳይቷል፡፡

በፎቶግራፉ ላይ እንደምታዩት፤ የሰራው ሞዴል፤ ‹‹የልጅ ሥራ›› አይመስልም፡፡ በቅርጹ ተመጣጣኝነት፤ በክሮቹ አደራደር እና አቆጣጠር ረቂቅነት፤ በሞዴሉ ጥንካሬ እና ሞዴሉን ለመስራት በተጠቀመባቸው ጥሬ እቃዎች እንደሚንጻባረቀው፤ የኪነጥበቡ ሥራ የጥበበኛ ሥራ ነው፡፡
 በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው፤ ኪነ ጥበቡ አየለ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሃይማኖት እና ባሕል ከሚያስተምረው መምህሩ፤ ዘማሪ የሻነው መኮንን ጋር የተነሳውን ፎቶ ነው፡፡

የኪነ ጥበቡን ሥራዎችን መነሻ በማድረግ፤ የደብሩ አዳጊዎች ክፍል፤ ወደፊት፤  በአዳጊዎች የተሰሩ ተመሳሳይ የእደ ጥበብ እና ፈጠራ ውጤቶችን ለምዕመናን የሚያሳይበት፤ ለሌሎች ልጆችም ማስተማርያ የሚያውልበት መላ እንደሚፈልግ ይጠበቃል፡፡

Monday, June 17, 2013

የመምህራን እና አስተባባሪዎች ጠቅላላ ውይይት

የአዳጊዎች ትምህርት ክፍል መምህራን እና አስተባባሪዎች፤ እሁድ ጁን 16 2013 ጠቅላላ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በውይይቱም የተሳተፉት አባላት ብዛት 12 ሲሆኑ፤ የተወያዩበት እና ያስተላለፉትም ውሳኔዎች ከሞላ ጎደል ይህንን የመስላሉ፡፡


1. የተዘጋጀውን ካሪኩለም ከልጆቹ አቅም/ ደረጃ/ ጋር ማጣጣምን በተመለከተ፡፡

በየክፍሉ ያሉ ተማሪዎች የቋንቋ እውቀት እና የእድሜ ደረጃ የተዘበራረቀ ስለሆነ፤ የተዘጋጀውን ካሪኩለም ለመተግበር እንቅፋት ሆኗል፡፡ ህይንን ለማስተካከል ሁለት ደረጃዎቸ ያሉት መፍትሔ ታስቧል፡፡
  •  ደረጃ አንድ፡፡ የሁለተኛው ሩብ ዓመት ፈተና ከተሰጠ በኋላ፤ ለፊደል ቤት፤ ንባብ ቤት ፤ እና መሠረተ ሃይማኖት ተማሪዎች አዲስ አይነት የክፍል ድልድል ማድረግ፡፡ይህም በተማሪዎች የቋንቋ እውቀት ላይ የተመሰረተ ድልድል ስለሚሆን፤ በአንድ ክፍል ውስጥ ተመጣጣች ችሎታ/ደረጃ/ ያላቸውን ልጆች ለማግኘት ይረዳል፡፡ ወላጆች ይህንን አስቀድመው እንዲያውቁትም ማስታወቂያ ደብዳቤ ተልኳል፡፡
  • ደረጃ ሁለት፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ፤ ካሪኩለሙ ለተማሪዎች ይመጥናል አይመጥንም የሚል ምዘና አድርጎ፤ የካሪኩለም ክለሳ ማካሄድ
2. የቴክስት ቡክ ዝግጅትን በተመለከተ

የአዳጊዎች ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የሚማሩበት፤ መምህራንም የሚያስተምሩበት ቋሚ ማስተማርያ መጽሐፍ/ ቴክስት ቡክ/ የለም፡፡ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን፤ የሚከተሉት ቴክስቶች እንዲዘጋጁ፤ ታስክ ፎርስ ተቋቁሟል፡፡
  • ቋንቋ ማስተማርያ ቴክስተ ቡክ፡፡ ይህንን እንዲያዘጋጁ የተመደቡት የታክስ ፎርሱ አባላት አቶ መኮንን፤ አቶ ካሰኝ፤ አቶ ናዖድ እና ወ/ሮ እመቤት ናቸው፡፡
  • የሃይማኖት ማስተማርያ ቴክስት ቡክ፡፡ ይህንን እንዲያዘጋጁ የተመደቡት የታክስ ፎርሱ አባላት፤ አቶ ዳንኤል፤ አቶ የሻነው እና አቶ ሰሎሎሞን ናቸው፡፡
ማሳሰቢያ፡፡ የሚዘጋጀት ማስተማርያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት፤ ለቤተክርስቲያን ቦርድ ቀርበው ከታረሙ እና ከተፈቀዱ ብቻ ነው፡፡

3. የአዳጊዎች መዘምራን በተመለከተ

  • በትምህርት ክፍሉ የታቀፉት ከ150 በላይ የሚሆኑ አዳጊ ልጆች፤ በየሳምንቱ እሁድ ከቅደሴ በኋላ መዝሙር የመያቀርቡበት መርሐ ግብር ተነድፏል፡፡ ይህንን ለማድረግ፤ ልጆቹ በየክፍላቸው የሚያጠኑት መዝሙር እና የሚያቀርቡ መዝሙር ዝርዝር እቅድ ተዘጋጅቶ፤ በቅርቡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ይለጠፋል፡፡
4. የቤተሰብ ቀን በዓል ዝግጅት

  • ተማሪዎች፤ ወላጆች እና መምህራን የሚተዋወቁበት እና የሚመካከሩበት አጋጣሚዎችን ማብዛት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፤ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ የቤተሰብ በዓል ቀን ተወስኖ፤ ልጆች ከወላጆቻው ጋር የሚታደሙበት፤ እየተዝናኑ የሚመካከሩበት መርሐግብር ይዘጋጃል፡፡ ይህም መርሐግብር በአቶ ቢኒያም እና በአቶ መሠረት አስተባባሪነት ይከናወናል፡፡
5. የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ወላጆ ለአዳጊ ልጆች ክፍል የሚሰጡት ድጋፍ ከአቅም በታች መሆኑን በተመለከተ እንዲሁም

6. የዓምደ ሃይማኖት ክፍል የመማር ማስተማር ሂደት ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች በተመለከተ ጥልቅ ውይይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

blessing

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡.......In The Name of The Father, The Son and The Holy Spirit. Amen.

Amen

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለ ወላዲቱ ድንግል፤ ወለ መስቀሉ ክቡር፤ አሜን::