Monday, January 6, 2014

ሁለተኛው ዙር የወላጆች እና መምህራን ጉባዔ ውጤት

 
በትናንትናው ዕለት እሁድ ጃንዋሪ 5 ቀን 2014 የወላጆች እና መምህራን ጠቅላላ ጉባዔ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ የጉባዔው ዋና ዓላማ አዲሱን የልጆች ትምህርት ቤት መዋቅር እና አሰራር ለማሳወቅ እና ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድሩ በጎፈቃደኛ ኮሚቴዎችን ማስመረጥ ነበር፡፡

መርሐግብሩ የተጀመረው በቤተክርስቲያኑ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ እስጢፋኖስ የመክፈቻ ንግግር ሲሆን፤ በንግግራቸውም ደብሩ ለአዳጊ ልጆች ትምህርት ቤት መጠናከር ያደረጋቸውን ጥረቶች እና በቅርቡ ለማድረግ የተዘጋጃቸውን ድጋፎች በአጭሩ ገልጸዋል፡፡ በገለጻቸውም

1.      ለትምህርት ቤቱ አስተባባሪ እና አስተማሪ የሚሆን ባለሙያ የመቅጠር ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር አሳውቀዋል

2.     ለትምህርትቤቱ እና ለተማሪዎች የሚያገለግሉ የመማርያ ቁሳቁስ (ወንበር እና ጠረጴዛ) ግዢ በቅርቡ እንዲከናወን አስታውቀዋል

3.     ደብሩ የልጆች ትምህርት ቤት የሚያደርገውን በጎ ጥረት ሁሉ የመደገፍ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል

ሁለተኛው መርሐግብር ለታዳሚዎች ስለ ትምህርትቤቱ ይዘት፤ ሥራዎችን እና ስለ ስብሰባው ዋና ዓላማ መግለጽ ነበር፡፡ ገለጻውን ያደረጉት የወቅቱ የአዳጊ ልጆች ትምህርትቤት ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት አካሉ ሲሆኑ በገለጻቸውም

1.      ትምህርትቤቱ ቢያንስ 189 አዳጊ ልጆችን መዝግቦ እንደሚያስተምር

2.     ትምህርትቤቱ የተጠና ሥርዓተትምህርት እንዳለው

3.     ትምህርትቤቱ የራሱ ድረ ገጽ እንዳለው

4.     ወላጆችን የሚያሳትፍ እና የትምህርቱን ጥራት የሚጨምር አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘጋጀቱን

5.     ትምህርትቤቱ ከደብሩ ቦርድ በቂ እና ቅን ድጋፍ እያገኘ እንደሆነ

6.     የዛሬው ስብሰባ ዓላማም በጎፈቃደኛ ወላጆች የሚያገለግሉበትን ዘርፍ እንዲመርጡ ማበረታታት እና አዲስ የትምህርት ቤት አስተዳደር ኮሚቴ ማስመረጥ እንደሆነ ገልጸዋል

ሦስተኛው መርሐግብር ስለ አዲሱ የትምህርት ቤቱ የአስተዳደር እና አደረጃጀት መዋቅር ማብራሪያ መስጠት እና ኮሚቴዎችን ማስመረጥ ነበር፡፡ ይህንን መርሐግብር የመሩት አቶ ናዖድ ቤተሥላሴ ሲሆኑ፤ በመርሐግብሩም ላይ

1.      የአዲሱን መዋቅር አስፈላጊነት፤ ይዘት እና አሰራር የተመለከተ ገለጻ አድርገዋል

2.     የትምህርት አሰጣጡ ወደ ክብ ጠረጴዛ ትምህርት እንደሚቀየር እና በክፍል ቢያንስ 5 ወላጅ መምህራን እንደሚያስፈልጉ

3.     ወላጆች ማገልገል የሚፈልጉበትን ክፍል ወይም ንዑስ ክፍል እንዲመርጡ እድል ሰጥተዋል

4.     በመጨረሻም በኮሚቴነት ማገልገል የሚፈልጉ ወላጆች ራሳቸውን እንዲጠቁሙ እድል ሰጥተው በጎፈቃደኞችን አስመርጠዋል

በመርሐግብሩ መጨረሻም ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከጥያቄዎቹም ውስጥ

1.      ስለሚቀጠረው መምህር አቀጣጠር እና መመዘኛዎች ምንነት ማብራሪያ ተጠይቋል

2.     ትምህርትቤቱ ቲነጀሮችን በመርዳት ዙርያ ለማድረግ ስላሰበው ጥረት አስተያየት እና ጥያቄ ተሰጥቷል

3.     ስለሚጀመረው የቱተር አገልግሎት አሰራር ማብራሪያ ተጠይቋል

4.     ተጀምሮ የተቋረጠው የጀማሪ ተማሪዎች ክፍል መቼ እንደሚጀመር ጥያቄ ተጠይቋል

5.     የማስተማርያ ቋንቋንም በተመለከተ አስተያየቶች ተሰጥተዋል

በመርሐግብሩ መጨረሻም ወላጆች ለአገልግሎት የመረጧቸውን ክፍሎች በተሰጣቸው ወረቀት ላይ አስፍረው የመለሱ ሲሆን፤ በውጤቱም 49 ወላጆቸ የመጀመርያ፤ ሁለተኛ እና ሦስተኛ የአገልግሎት ምርጫቸውን አሳውቀዋል፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታትም፤ በኮሚቴነት ለማገልገል ፈቃደኝነታቸውን የገለጹ ወላጆች ተሰባስበው፤ ዋና አስተባባሪያቸውን ይመርጣሉ፡፡ ሙሉ ዝርዝሩንም ለቦርድ ያሳውቃሉ፡፡
 

blessing

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡.......In The Name of The Father, The Son and The Holy Spirit. Amen.

Amen

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለ ወላዲቱ ድንግል፤ ወለ መስቀሉ ክቡር፤ አሜን::